ትንኝን
ማጥራት ግመልን መዋጥ ማቴ 23
- ሁሌ እኔ ቤተክርስቲያን ሳለስቀድስ ስቀር ተቸግሬ ነው::ሌላው ሠው ሲቀር ግን ደካማ ለቤተክርስቲያን ቀናኢ አስተሳሰብ የሌለው ሆኖ ነው::
- ሠውን ሳማና ስተች ከእውነት ከልብ ከመነጨ ቅን አስተሳሰብ ነው::ሌሎች ሲሆኑ ግን ሐሜቶኞች ወሬኛ ሠው አናጋሪ ነገር ለቃሚዎች ናቸው::
- እኔ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስስቅ ስቀልድና ስዘልፍ ከጓደኛዬ ጋር እየተጫወትኩኝ ነው::ሌሎች ሲሆኑ ግን የቤተክርስቲያን ህግ እና ሥርዓት እየጣሱ ነው::
- እኔ ሳልጻም ሳልጸልይ ቤተ እግዚአብሔር ሳልሄድ ሳልሰግድ ስቀር ሕመሜን የልቤን ችግር እግዚአብሔር ተረድቶት ነው::ሌሎች ሲሆኑ ግን ሰነፎች አስመሳይ ክርስቲያኖች ሆነው ነው::
- እኔ ጠጥቼ ስሰክር ስዳንስ ስጨፍር ሳጨስ ትንሽ የሥጋ ድካም ተሰምቶኝ ነው::ሌሎቹ ሲሆኑ ግን የቤተክርስቲያን ማንነት አሰዳቢ ናቸው::
- እኔ ጠንቆይ ቤት ስሄድና ሳስጠነቁል ጨሌ አቴቴ ሳደርግ ፅንስ ሳስወርድ ጨንቆኝ የማደርገው ጠፍቶኝ ነው::ለሎች ሲሆኑ ግን ጣኦት አምላኪዎች ነፍሰ ገዳዬች ናቸው::
- እኔ ሳመነዝር የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ ጥረት እያደረኩ ነው::ደግሞም እኮ እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙላአት የሚለውን ቃል እየፈጸምኩኝ ነው:: ሌሎች ሲሆኑ ግን ሴሰኛ ሆነው ነው::
- እኔ ለድሃ ምፅዋት ስሰጥ ራርቼ አዝኜ ችግራቸው የእኔ ችግር ሆኖ ነው::ሌሎች ሲሆኑ ግን ሀብታቸውን ንብረታቸውን ለሰው ሊያሳዩ ለታይታ ነው::
- እኔ ጉቦ ስበላና ስሰርቅ ቸግሮኝ ኑሮዬን ለማሸነፍ ጥረት እያደረኩ መሆኑን እግዚአብሔር የልቤን ችግር ስለሚያውቅ ነው:: ሌላው ግን ጉቦኛ ሌባ ሆኖ ነው::
- እኔ ስጾም ስጸልይ ጻድቅ ትሑት ሆኜ የእግዚአብሔር ፍቅር አሸንፎኝ ነው::ሌላው ሠው ሲሆን ግን የሚሠራውን ሲያጣ የረሃብ አድማ በራሱ ላይ እያደረገ ነው::
- እኔ ጠዋት እንቅልፍ ይዞኝ ሥርዓተ-ቅዳሴ እንደተጀመረ ቤተክርስቲያን ስገባ ምንም አይደለም እግዚአብሔር እንደ ደከመኝ ያውቃል::ሌላው ሲሆን ግን የእግዚአብሔርን መላእክት እየረገጠ መግባቱና ሥርዓት ማፍረሱ ነው::
- እኔ ቤተእግዚአብሔር ጉባዔ ስቀር በጣም ሥራ በዝቶብኝ ጊዜ አጥቼ ነው::ሌሎች ሲሆኑ ግን ከእግዚአብሔር እየራቁና አየሰነፉ መምጣታቸው ነው::
- እኔ ቤተክርስቲያን ቀርቼ ሠርግ ድግስ ዘመድ ጥየቃ ስሄድ ሠው ብቻውን ያለሠው መኖር እንደማይቻል ራሱ እግዚአብሔር ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ነው::ሌሎች ሲሆኑ ለቤተክርስቲያን ቅናት ተቋርቋሪነት ፈፅሞ የሌላቸው ከንቱዎች ሆነው ነው::
ታዲያ
የራስን ኃጢያት በመልካም ሥም ከማሞካሸት ተመልሼ የሌላውን ኃጢያት በባትሪ ፈልጌ ከመንቀስ ተቆጥቤ ግመልን ውጬ ትንኝን አጥርቼ ትንሿን የአፈር ክምር ተራራ ማሣከል ትቼ ራሴን ማስተካከል እንድጀምር እግዚአብሔር ይርዳኝ::
የማቴዎስ ወንጌል 23
“በዚያን
ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።እናንተ ግን። መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።እናንተ። ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ።እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።
እናንተ
ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ።አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል እናንተ ግብዞች
ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና።በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።”