ምንም በደል ቢኖር
ኃጢአትም ቢበዛ
የመታዘዝ ፍሬ
ከሰዎች ቢታጣ
የፅድቅ ሥራ ጠፍቶ
አመፅ ቢበረታ
አንተ ባለህበት ---
በዚያ ምህረት አለ
ኩነኔም የለበት
የሚያስደንቅ ማዳን
ፍቅር የሞላበት
የይቅርታ ጉዞ
ፅድቅ የሰፈነበት
--- ምን ጠላት ቢበዛ
ኃይሉም ቢበረታ
ቀንበሩም ቢፀና
ቢበዛም ሁካታ
አስፈሪ ነበልባል
እጅግ ቢንበለበል
ውኃውም ቢፈላ
ቢፍለቀለቅ በኃይል
የኤርትራ ባህር
በሰፊው ቢንጣለል
ወደ አንበሶች ጉድጉዋድ
ቢኖር እንኳን መጣል
አንተ ባለህበት ---
ጠላት ይሸነፋል
የእብሪቱ ድልድይ
በቃልህ ይናዳል
ነፃነት ታውጆ
ቀንበሩም ይነሳል
ፍል ውሃው ቀዝቅዞ
እሳቱም ይጠፋል
ባህሩ እንደተራራ
ቀጥ ብሎ ይቆማል
ጠላት ከነጀሌው
በውሃ ይበላል
ውሃ ውስጥ ይሰጥማል
የአናብስቱም አፍ
በኃይልህ ይዘጋል
--- ነውጡ እጅግ ቢያይል
ማእበል ቢነሳ
ተስፋ መቁረጥ ነግሶ
ቢበዛም አበሳ
አንተ ባለህበት ---
ይታዘዛል ባህሩ
ነውጡም ያጣል ኃይሉን
ጸጥ ይላል ማእበሉ
--- አሳዎች በባህር
አንዳችም ባይኖሩ
መረቡም ባይሞላ
ድካም ቢሆን ትርፉ
አንተ ባለህበት
ማጣት የለም ከቶ
ረሃብ ይወገዳል
አሳው ተትረፍርፎ
መረቡም ሞልቶ
--- ህመም ደዌ ጸንቶ
ሕይወት ብትደበዝዝ
አስታማሚ ጠፍቶ
ባይኖርም የሚያግዝ
አንተ ባለህበት ---
መድሃኒት መች ጠፍቶ
የማያየው ሁሉ
ይመለሳል አይቶ
በደስታ ይቦርቃል
ለምፃሙ ሰው ነፅቶ
ዲዳው ይናገራል
ይጮሃል አብዝቶ
--- ምን ሞት ቢበረታ
ቢያይል ፍርሃቱ
ብቸኝነት ነግሶ
ቢበዛ ጭንቀቱ
አንተ ባለህበት ---
ሞት ስልጣኑን ያጣል
ማንቀላፋት የለም
የሞተም ይነሳል
ሀዘኑ በደስታ
ሞትም በትንሣኤ
በአንተ ይለወጣል
ስለዚህ ጌታ ሆይ
በአንተ ሁሉ ካለ
የአንተ ልሁንና
ሁሉን ላግኝ ከአንተ
መቅደስ አያሌው (ከደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን)