ESMEBEFKADU

Friday, December 30, 2011

ለእኔስ እንደ ስሟ


ቢያበሉኝ ቢያጠጡኝ ፈትፍተው ቢያጎርሱኝ
ያየሁትን ሁሉ አምጥተው ቢሠጡኝ
ከሥጋ አይነቶች ብላ ፍራፍሬን  
ጠጥተህም እርካ ብላ ያማረህን 
ያሻኸውን ብላ ሁሉ ያንተ ቢሉኝ
ለእኔስ እንደ ስሟ የጣፈጠ አጣሁኝ
ስሟንም ጠርቼ በላሁኝ ጠጣሁኝ
ስለማርያም ብዬ ሁሉን አገኘሁኝ
አገኘሁ ምህርትን በላሁኝ ጠጣሁኝ
ስለ ድንግል ብዬ ፍጽም አላፈርኩኝ
በአማላጅነቶ ምህረት አገኘሁኝ
ለእኔስ እንደ ስሟ የጣፈጠ አጣሁኝ
ለእኔስ እንደ ስሟ የጣፈጠ አጣሁኝ
ለእኔስ እንደ ስሟ የጣፈጠ አጣሁኝ

መድኅን ተወልዶላችኋል

መድኅን ማለት አዳኝ ወይም መድኃኒት ማለት ሲሆን ይህም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ቤዛ ስለሆነ ቀደም ብለው ነቢያት ትንቢት ሲናገሩለት ቆይተው ነበር ከዚህም የተነሳ መድኅን የተባለው ቃል ለረጅም ዘመናት በተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ስለነበረ በተፈጸመ ጊዜ ሁሉ ነገር ታደሰ፡፡ የዳዊት ከተማ በነበረችው በቤተልሔም የዘመኑ ፍጻሜ ደረሶ መድኃኒትነቱ በነቢያት የተነገረለት መድኅን ክርስቶስ በመወለዱ ከመርገም በታች ወድቆ ይኖር የነበረውም የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገረ፡፡ በኃጢአት አርጅቶ የነበረው አሮጌው ዓለም መልኩን ለውጦ አዲስ ሆነ፡፡ ከዚህ በፊት ተደረጎ የማያውቀውና ወደፊትም ሊደረግ የማይታሰበው ረቂት ምሥጢር በመገለጹ የሰማይ መላእክትና በሌሊት መንጋቸውን አሰማርተው ይጠብቁ የነበሩት እረኞች «ሰላም በምድር እርቅም ለሰው ልጅ ይሁን» እያሉ በኅብረት ዘመሩ፡፡ ለሰው ልጆች ታላቅ ደስታና ሰላም ተፈጽሟልና፡፡ 


ይሁን እንጂ መድኅን ክርስቶስ ከመወለዱና ለሰው ልጆች ይህን የመሰለው ታላቅ ደስታና ሰላም ከመገኘቱ በፊት የነበሩ አንዳንድ የአረማውያን ገዢዎች ራሳቸውን ማዳን ሳይሆንላቸው መድኅን የተባልን እኛ ነን ለራሳቸው የኅሊና ረፍትና የልብ ሰላም ሳያገኙ ለሌላው ሰላም እናስገኛለን እያሉ የተወለዱበትን የልደት ቀን ያከብሩና ያስከብሩ ነበር፡፡


ያልተማረውና ዕውቀት ያነሰው ሕዝብ የተናገሩት እውነት እየመሰለው ሰላም ያስገኙልናል መድኅኖቻችን እነሱ ናቸው በማለት የተወለዱበት ቀን በሚከበርበት ጊዜ የታሠረ ለምለም ቄጤማ ፣የዘንባባ ቅጠል፣ የወይራ ዝንጣፊ ሲያቀርብላቸው እቅፍ አበባ ሲያበረክትላቸው ኖሮአል፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው ከፈርዖኖች መካከል የተወለደበትን ቀን ሲያከብር ያደረገውን እንመልከት «በሦስተኛው ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ይከብር ነበር ለሠራዊተም ሁሉ ግብር አደረገ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎችን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ፡፡ የጠጅ አሳላፊዎችንም አለቃ ወደ ሥፍራው መለሰ፡፡ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፡፡ የእንጀራ አበዛዎችንም አለቃ ሰቀለው» ኦሪት ዘፍጥረት 40-20-22 መድኅን ነኝ ለሕዝቡ ሰላም እሰጣለሁ እያለ የሚመካው ፈርዖን የተወለደበትን ቀን በሚያከብርበት ጊዜ እስረኛን በመፍታት ለተበደለው ይቅርታ በማድረግ ፋንታ እንጀራ አሳላፊውን ሰቅሎ የወፎች ምግብ እንዲሆን አደረገው፡፡ በዘመኑም የፍርድ ጉድለትና አድልዎ የርስ በርስ መለያየት ስለነበር በሕዝቡ ዘንድ ሰላም አልነበረም ሰባት ዓመትም ታላቅ ረኀብ ሆኖ በህዝብ ዘንድ ታላቅ ችግር በመድረሱ መድኅን የተባለው ቃል በተግባር ሳይተረጎም ቀርቶአል፡፡ 


በሌላ በኩል ደግሞ የገሊላ ገዢ የነበረውን የሄሮድስን ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ የተወለደበት የልደቱን በዓል በሚያከብርበት ቀን ለተራቡት ሳይሆን ለመኳንንቱና ለመሳሰሉት ታላቅ የምሳ ግብዣ አደረገ፡፡ በግብዣውም መካከል የዘፈነችው ዘፋኝ ስላስደሰተችው የጠየቀችውን ሊሰጣት ተስፋ ሰጣት እሷም የባህታዊውን የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ ቆርጦ እንዲሸልማት ጠየቀችው፡፡ ግብዙ ሄሮድስም ልዩ ልዩ የጌጥ ሽልማት ሊሸልማትና የገንዘብ ስጦታ ሊያደርግላት ሲገባው ፍርድ የሚጠባበቀውን የእስረኛውን የዮሐንስን ራስ ቆርጦ ሸልማት ማቴዎስ ወንጌል 14-5-10፡፡


ይህን የመሰለውን ግፍ በመፈጸሙ ልደቱ የሰላም የጤንነት የክብር ልደት መሆኑ ቀርቶ የስቃይ ልደት ሆነ፡፡ በህዝብም ዘንድ ሰላም ፍቅር ጠፍቶ መለያየትና ሁከት ተፈጠረ ሄሮድስም መድኅን መባሉ ቀርቶ ግፈኛ ነፍሰ ገዳይ የሚለውን ስም ትቶ አለፈ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የተወለደው ለተራበው ዓለም እንጀራ ሆኖ ለመቅረብ ነው፡፡ ራሱ ድኃ ሆኖ ድሆችን ባለጸጋ ለማድረግ ነው ይህንንም ለመፈጸም አምላክና ጌታ ሲሆን በከብቶች በረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ልብሱ እሣት እየተባለ የሚነገርለት እሣት መለከት በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኛ ይህንንም በማድረጉ የሰው ፍቅር አገብሮት ለሰላምና ለፍቅር መምጣቱን በተግባር አስመሰከረ፡፡ 


ካቢር የተባለው ፈላስፋ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆንና መወለድ የሚከተለውን ተናግሮአል «በወንዝ ዳር ሁለት ካህናተ ጣዖትን አገኘ ሰማይና ምድርን ዓለማትን የፈጠረ አንድ አምላክ እያለ ለምን እናንተስ ብዙ ጣኦትን ታመልካላችሁ ሕዝቡንስ በእነሱ እንዲያመልክና እንዲያምን ለምን ታደርጋላችሁ ቢላቸው እኛና አባቶቻችን ሲወርድና ሲዋረድ በመጣው መሠረት ስናምን የቆየነው በብዙ አማልክት እንጂ በአንድ አምላክ አይደለም አሉት፡፡ ነገሩን ባትገነዘቡት ነው እንጂ ፀሐይ እስኪወጣ ድረስ ጨረቃና ከዋክብት እንደ ፀሐይ ሙሉ ብርሃን ሰጥተው ሊያበሩና ሊሞቁ አይችሉም፡፡ ስለዚህም እናንተ የምታመልኩዋቸው ጣኦታትም የሱ ስነፍጥረትና ስው ሰራሾች ስለሆኑ የሰውን አዕምሮ ከማጨለም በቀር እንኳንስ ለሌላው ብርሃን መስጠታቸው ቀርቶ ለራሳቸው ብርሃን የላቸውም እንደ ፀሐይ ብርሃን የሚሰጠውና ፀጋ የሚያድለው እውነተኛው አምላክ ወደፊት ሰው ሆኖ ይወለዳል መድኅንም ሆኖ ዓለምን ሁሉ ያድናል እሱም በተወለደ ጊዜ ጣኦታት ሁሉ ይጠፋሉ ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ ትንቢቱም ተፈጽሞ እውነተኛ መድኅን የሆነው አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ 


ኢሳይያስም እነሆ ድንግል ትፀንሣለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፡፡ አለቅነቱም በጫንቃው ላይ ይሆናል የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል ሲል ትንቢት የተነገረለት አማኑኤል በተወለደ ጊዜ ጣኦታት ይጠፋሉ ሲል ተንብዮ ነበር፡፡ ትንቢቱም የሚለው የሰው ኩራቱ ይወድቃል በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ይላል ጣኦቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው ይጠፋሉ በዚያም ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁዋቸውን የብሩንና የወርቁን ጣኦቶቹን ለፍልፈልና ሌሊት ወፍ ይጥላሉ ትንቢተ ኢሳይያስ 2-16-20፡፡


እንዳለውም መድኅን ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ በከንቱ ይመለኩ የነበሩት ጣኦታት ሁሉ ጨርሰው ጠፉ ስለዚህም ወንጌላዊው ሉቃስ በጻፈው ወንጌል እንደምንረዳው «እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ» በማለት መልአኩ ለእረኞቹ እንዳበሠራቸው ሉቃስ 2-8-12 ይናገራል፡፡ 


ዛሬም ቢሆን ስለ ዓለም ሰላም የተወለደው መድኅን ክርስቶስ አትፍሩ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ እያለ በቤተክርስቲያን አማካኝነት ይናገራል፡፡ ዓለም ግን በገዛ እውቀቱና በገዛ ጥበቡ በራሱ ገንዘብና በራሱ ጉልበት እየተመካ በክርስቶስ ሰላም አልተጠቀመም፡፡ 


ይኸውም ዓለም በኃጢአት በተንኮል እርስ በርሱም በመጨካከን ለአንተ ከማለትም ይልቅ ለእኔ በማለት ወደ ጥፋት ሲያዘነብል ይታያል፡፡ ለሰላም ከሚያወጣው ገንዘብ ይልቅ ለጦርነት የሚያወጣው ወጭ አሥር እጥፍ በመሆኑ ድህነትንና በሽታን፣ ድንቁርናን በመቃወም ፈንታ አንዱ ለሌላው መቅሰፍት በመሆን እልቂት በመፍጠር ፍቅር እየቀዘቀዘ ስለሄደ ጣፋጭ የነበረውን ዓለም መራራ አድርጎታል፡፡ 


በዓለም ሰላም እንዲበዛና መራራ የሆነው የሰው ልጅ ኑሮ እንዲጣፍጥ የመድኅን ክርስቶስን ልደት በመንፈሳዊ ስሜት እንድናከብር ያስፈልጋል ምክንያቱም በዓለም ላይ ብዙ የደስታ ልውውጦች እንደ ተደረጉ እናውቃለን የክርስቶስ ልደት ግን የሥጋን ብቻ ሳይሆን የመንፈስንም ለውጥ አስተባብሮ የያዘ በመሆኑ ምእመናን ለሆን ሁሉ አዲስ ለውጥ ሆኖልናል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስን ልደት ስናከብር አዲስ ልብስን በመልበስ ብቻ ሳይሆን በአዲስ መንፈስ በአዲስ ልብ እናክብረው፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እስመ በፈቃዱ

"እስመ በፈቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኅነነ"ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ